
ለጎርፍ አደጋ ተጋላጭ ተብለዉ በተለዩ ቦታዎች አደጋውን ለመከላከል የሚያስችሉ የማቅለያ ስራዎች እየተከናወኑ እንደሆነ በም/ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ወንድሙ ሴታ አስታወቁ።
ለጎርፍ አደጋ ተጋላጭ ተብለዉ በተለዩ ቦታዎች አደጋውን ለመከላከል የሚያስችሉ የማቅለያ ስራዎች እየተከናወኑ እንደሆነ በም/ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ወንድሙ ሴታ አስታወቁ።
በአዲስ አበባ ከተማ ለጎርፍ አደጋ ተጋላጭ ተብለዉ በተለዩ ቦታዎች እየተከናወኑ ያሉ የማቅለያና የመፍትሄ እርምጃዎች የደረሱበትን ደረጃ ለመገምገም በም/ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጅነር ወንድሙ ሴታ የተመራ በቅንጅት የጎርፍ መከላከልን ስራ እያከናወኑ ያሉ የከተማ አስተዳደር የሴክተር ተቋማትና የተጠሪ ተቋማት እንዲሁም የክፍለከተሞች አመራሮች በተገኙበት ዛሬ ግንቦት 19 ቀን 2017 ዓ.ም የመስክ ምልከታ ተካሂዷል።
በመስክ ምልከታው ማጠቃለያ ላይ ኢንጂነር ወንድሙ ሴታ እንደተናገሩት ለአደጋ ተጋላጭ ተብለዉ በተለዩ ቦታዎች እየተወሰዱ ያሉ የማቅለያና መፍትሄ የመስጠት ስራዎች እየተጠናቀቁ መሆኑን ጠቅሰዉ ያልተጠናቀቁ ቀሪ ስራዎች የክረምቱ ጊዜ ሙሉ በሙሉ ከመግባቱ በፊት ባሉት ጥቂት ጊዚያት አስቀድሞ ለማጠናቀቅ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል።
አያይዘዉም በተለይም ኑሯቸዉን በወንዝ ዳርቻ ያደረጉና ለአደጋ ተጋላጭ የነበሩ ነዋሪዎችን ከአደጋ ወደተጠበቀና ምቹ ወደሆነ አካባቢ መዘዋራቸዉንና ቦታዉም በወንዝ ዳርቻ ልማት ታቅፎ እየለማ መሆኑን ጠቅሰዉ ለጎርፍ አደጋ ምክንያት የሚሆኑ የፍሳሽ መስመሮችን በተለያዩ ባዕድ ነገሮች ባለመዝጋትና ሊያጋጥሙ የሚችሉ አደጋዎችን ለመቀነስ በሚደረገዉ ጥረት ህብረተሰቡ እንደ ከዚህ ቀደሙ ተባባሪ በመሆን የመፍትሄዉ አካል እንዲሆንም አሳስበዋል።
በመስክ ምልከታዉ በአቃቂ ፣ በነፋስ ስልክ፣ በአዲስ ከተማ፣ ቂርቆስ እና በአራዳ ክፍለ-ከተሞች ባሉ እየተከናወኑ ያሉ የጎርፍ መከላከልና የማቅለያ ስራዎች የተጎበኙ ሲሆን በጉብኝቱም የሴክተር ተቋማት፣ የክፍለ-ከተሞች ዋና ስራ አሰፈጻሚዎችና ስራ አስኪያጆች ፣ የእሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽንና የአካባቢ ጥበቃ እንዲሁም የጽዳት አስተዳደር ኤጀንሲ ስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
ለእሳትና ለሌሎች ድንገተኛ አደጋዎች እንዲሁም ለአንቡላንስ አገልግሎቶች በ939 ፈጥነዉ ያሳዉቁ!